የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ እና ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ እና ሙስናን ለመዋጋት የአለም አቀፉ ጥምረት አካል የሆነው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋራ መስራት የሚያስችለቸውን የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ የተቋማቱ ከፍተኛ ሀላፊዎች በተገኙበት ተፈራረሙ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ እና ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በጋራ ለመስራት የተስማሙበት ፕሮጀክት “በኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ትግሉን ለመደገፍና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርና የህግ የበላይነትን ለማስፈን በተቋማት ውስጥ ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲቻል የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ” የሚል ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮን በመወከል የቢሮው ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ጽዋዮ ሙሉነህ ሲሆኑ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናልን በመወከል ደግሞ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሳሙኤል ካሳሁን ናቸው፡፡

በስምምነት ሰነዱ ላይ እንደተገለፀው ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚደረገው በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ባህርዳር እና መቀሌ ከተሞች ሲሆን በእነዚህ ከተሞች የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች፣ ከከተሞቹ አስተዳደር፣ ከስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች፣ ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተጠቅሷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ እና በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መካከል በአዲስ አበባ ከተማ በዋነኝነት የሚሰራው ስራ የንቃተ-ህግ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እና ለተለያዩ ጉዳቶች ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎትን መስጠት ላይ ሲሆን

ይህም የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ በሚገባ አጉልቶ እንዲሰማ ለማስቻል እና ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል፡፡